(ቢሊሱማ, 11 October 2011) በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ ተጀምሮ በተጠናቀቀው የኢነርጂ ኮንፈረንስ ላይ እየተሳተፉ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ሰዎች ተቃውሞ ገጠማቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገጠማቸውን ተቃውሞ ሲያጣጥሉት፣ ተቃዋሚዎቹ ያነሷቸውን አንዳንድ ነጥቦች እንደሚቀበሉ የኖርዌይ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል፡፡
‹‹የኖርዌይና የሌሎች አገሮች ድርጅቶች በአፍሪካ አገሮች ፖለቲካ ጣልቃ የመግባት መብት ያላቸው ይመስላቸዋል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በተመሳሳይ እኔ እንደ ኢትዮጵያዊነቴ በእነሱ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት መብት የለኝም፡፡ በመሆኑም ይኼ ተገቢ ያልሆነ ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ተቃዋሚዎቹ ድጋፋቸውንም ሆነ ተቃውሞአቸውን የመግለጽ መብት አላቸው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ ‹‹ይህ ደመና ነው መጥፋቱ አይቀርም፤›› ብለዋል፡፡
በስብሰባው ወቅት ተቃውሞአቸውን ለመግለጽ የተገኙት ሰዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰትና እስራት በኢትዮጵያ እየተባባሰ መጥቷል በማለት ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡ በአንፃሩ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ከማስመዝገቧም በላይ መልካም አስተዳደር እየሰፈነባት መሆኗን ገልጸዋል፡፡
‹‹ከባዶ ነው የተነሳነው፡፡ በቀድሞው ሥርዓት ዜጎች ተገድለው ቤተሰቦቻቸው ለተገደሉበት የጥይት ሒሳብ እንዲከፍሉ ይገደዱ ነበር፤›› በማለት፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ የሰነፈነባት አገር መሆኗን አስታውቀዋል፡፡
የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር የንስ ስቶልተንበርግ ግን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በአፍሪካ ዕድገትንና መረጋጋትን በማስተዋወቅ ረገድ ተጠቃሽ መሪ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡