ቅሬታቸውን ያቀረቡ ነዋሪዎች እየታሰሩ ነው

(ቢሊሱማ, አርባ ምንጭ, 16 October 2011) በመሬት ዘረፋና በመልካም አስተዳደር ችግር እየተሰቃየን ነው በሚል ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቅሬታ ያቀረቡ የአርባ ምንጭ ዙርያ ነዋሪዎች፣ እየታሰሩ መሆኑን ከአካባቢው የወጡ መረጃዎች አመለከቱ፡፡

በእስካሁኑ ሒደት ቅሬታ ካቀረቡ 548 በአርባ ምንጭ ዙርያ የላንቴ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል 60 ሰዎች የታሰሩ ሲሆን፣ የእነዚህ ነዋሪዎች ቅሬታ እውነት መሆኑን በጥናት ካረጋገጡ ባለሙያዎች መካከል ሁለቱ ከሥራ ታግደው ታስረዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ዕትም በመሬት ወረራና በመልካም አስተዳደር እጦት የተበሳጩ የቀበሌው ነዋሪዎች፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ቅሬታ ማቅረባቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎቹ የታሰሩት ካድሬዎች የአካባቢውን መሬት መቀራመታቸውን በመግለጻቸው መሆኑን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፡፡

ይህንን ተከትሎ ለምን ይህንን ጉዳይ አሳልፋችሁ ተናገራችሁ፣ ሕዝብን በመንግሥት ላይ አሳምፃችኋል በሚል የጋሞ ጎፋ ዞንና ወረዳ ቅሬታ አቅራቢዎቹን በሕገወጥነት በመፈረጅ እንዲታሰሩ ትዕዛዝ አውጥቷል፡፡

በእስካሁኑ ሒደት በአርባ ምንጭ ከተማ፣ በአርባ ምንጭ ዙርያና በላንቴ ፖሊስ ጣቢያዎች 60 ቅሬታ አቅራቢዎች መታሰራቸው ተረጋግጧል፡፡

ከክልል ተወክለው ከመጡ ሦስት ባለሙያዎች መካከል የነዋሪዎቹን ቅሬታ ትክክል ስለመሆኑ እንዲያጠኑ የታዘዙ ሁለት የወረዳው አስተዳደር ባለሙያዎች ከሥራቸው ከታገዱ በኋላ፣ ባለፈው ዓርብ መታሰራቸውን ከስፍራው የደረሱን መረጃዎች አረጋግጠዋል፡፡

ምንጮች እንደገለጹት፣ መሬቱን የወረሩት ከቀበሌ እስከ ክልል ደረጃ ያሉ ካድሬዎች አመራሮች ናቸው፡፡ ‹‹ለምን ተነካን ብለው ነው ነዋሪዎችን የሚያስሩት፤›› ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ምሬታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የላንቴ ቀበሌ በአርባ ምንጭ ዙርያ ከሚገኙ ሦስት ቀበሌዎች አንዱ ነው፡፡ በቀበሌው 967 አባወራዎች ሲኖሩ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅሬታቸውን ያቀረቡት 548 ነዋሪዎች ናቸው፡፡

ነዋሪዎቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅሬታ ለማቅረብ የተገደዱት ችግራቸውን ዞኑና ክልሉ ሊፈቱት ባለመቻላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የነዋሪዎቹ ዋነኛ ቅሬታ እንደሌሎች የአገሪቱ ክልሎች በ2000 ዓ.ም. መንግሥት በሁሉም አካባቢዎች የሚሊኒየም ፓርክ እንዲከልልና እንዲለማ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

በዚህ ጥሪ መሠረት የላንቴ ነዋሪዋች የሚሊኒየም ፓርክ እንዲከለል ማድረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ይህንን ቦታ ለካድሬዎችና ለባለሥልጣናት ተሰጥቷል በሚል ነው የመጀመርያው ቅሬታ የቀረበው፡፡

የሚቀጥለው ቅሬታም ለዘመናት ሲጠበቅ የኖረ የደን ክልልም እንዲሁ ለግለሰብ የተሰጠ ሲሆን፣ ግለሰቡም ከሰል እያከሰለበት ነው፡፡ ይህ ደን ሲመነጠር በአካባቢው የሚገኘው የባሶ ወንዝ ጥፋት ያደርስብናል ብለዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ከዚህ በተጨማሪም በቀበሌው መልካም አስተዳደር ካለመኖሩም በላይ፣ በሥልጣን ላይ የተቀመጡት አመራሮች ግለኞችና እምነት የማይጣልባቸው ናቸው ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡

እነዚህ ነዋሪዎች በተለያዩ ጊዜያት ለወረዳውና ለዞኑ ቅሬታቸውን ሲገልጹ በማሳቸው ላይ ጥፋት እንደሚፈጸምባቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ቅሬታ ገልጸዋል፡፡

ምሬታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጻቸውን ተከትሎ የበቀል ዕርምጃ እየወሰደባቸው ከመሆኑም በላይ ነዋሪዎቹ እየታሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በርካታ ወጣቶችም ይህንኑ በቀል በመስጋት ከአካባቢው እየተሰደዱ መሆኑን ከነዋሪዎቹ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡
source: http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/3759-2011-10-15-13-04-06.html

By bilisummaa