(ቢሊሱማ,ጥቅምት 22 ቀን 2011)የቀድሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩትና በአሁኑ ወቅት የተወካዮች ምክር ቤት አባልና የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ያረጋል አይሸሹም፣ ያለመከሰስ መብታቸው ተነሳ፡፡
አቶ ያረጋል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑና በሁለተኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ ያለመከሰስ መብታቸውን ያነሳው የሕግ፣ የፍትሕና የአስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን ጠቅሶ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ ባስተላለፈው ሙሉ ድምፅ ነው፡፡
አቶ ያረጋል የክልሉ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ጊዜ በክልሉ እንዲሠሩ በጀት ከተያዘላቸው ሦስት ትምህርት ቤቶች ላይ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ጋር በመመሳጠር ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው በማስረጃ በመረጋገጡና በቂ አመላካች ነገሮች በመኖራቸው ነው ተብሏል፡፡ በዚህም ምክንያት ያለመከሰስ የሕግ ከለላቸው እንዲነሳ ተወስኗል፡፡
ተጠርጣሪው አቶ ያረጋልን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችለውን የምርመራ ሥራ ለማከናወን በሚመለከተው መንግሥታዊ አካል የቀረበው የሕግ ከለላን የማንሳት ጥያቄ፣ በቋሚ ኮሚቴው ተቀባይነትን በማግኘቱ የሕግ ከለላቸው እንዲነሳ የውሳኔ ሐሳብ መቅረብ መቻሉ በቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ተገልጿል፡፡