(ቢሊሱማ,ጥቅምት 24 ቀን 2011)“የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጉዳዩን የማየት ሥልጣን የለውም” አቶ ያረጋል አይሸሹም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለመከሰስ መብታቸውን ጥቅምት 7 ቀን 2004 ዓ.ም ማንሳቱን ተከትሎ፣ የቀድሞው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክስ ፕሬዚዳንት አቶ ያረጋል አይሸሹም ጥቅምት 9 ቀን 2004 ዓ.ም በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ፣ ጥቅምት 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ያረጋልን በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ፖሊስ ነው፡፡
የኮሚሽኑ መርማሪ ፖሊስ ጥቅምት 10 ቀን 2004 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት አቅርቧቸው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆባቸዋል፡፡
መርማሪው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የሚጠይቅበትን ምክንያት ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዳ፣ “ተጨማሪ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ይቀሩናል፡፡ ተጠርጣሪው በዋስ ቢለቀቁ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን በመሆናቸው፣ ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም ማስረጃ ሊያስጠፉብን ይችላሉ፡፡ ዓቃቤ ሕግ የሚመሠረትባቸው ክስ ዋስትና የሚያስከለክል በመሆኑ የጠየቅነው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይፈቀድልን፤” ብሏል፡፡
አቶ ያረጋል በቁጥጥር ሥር በዋሉበት ጊዜ የደረሰባቸው ችግር ካለ ተጠይቀው፣ “ምንም ችግር አልደረሰብኝም፤ የተጠረጠርኩበት ጉዳይ የፌዴራል ሳይሆን የክልል ጉዳይ ነው፤ በመሆኑም ጉዳዩን መመልከት የሚችለው የክልሉ የፀረ ሙስና ኮሚሽን እንጂ፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አይደለም፡፡ የማየት ሥልጣንም የለውም፤” ብለዋል፡፡
የ41 ዓመት ዕድሜ ጐልማሳና የአራት ልጆች አባት መሆናቸውን የገለጹት አቶ ያረጋል፣ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ሲያቀርብ በእሳቸው ላይ የሚፈለገው ማስረጃ ተሰብስቦ ማለቁ የተነገረ በመሆኑ፣ ፖሊስ አሁን በድጋሚ “ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ” የሚለው ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ፣ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን አቶ ያረጋል ያነሷቸው ጥያቄዎች ክስ ሲመሠረት በፍሬ ጉዳይነት የሚቀርቡ መሆኑን በመግለጽ፣ መርማሪው ባቀረባቸው ማስረጃዎች ላይ ፍርድ ቤቱም የተገነዘበው ነገር መኖሩን አስረድቶ፣ ተጠርጣሪው እስከ ጥቅምት 21 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ በማዘዝ የተጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል፡፡
ኮሚሽኑ አቶ ያረጋል በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ከ2003 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ ባደረገው ክትትልና ማጣራት የፌዴራል መንግሥት በሰጠው የበጀት ድጎማ፣ በ1998 ዓ.ም የጣና በለስ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት፣ የግልገል በለስ መምህራን ኮሌጅንና የአሶሳ መለስተኛ ቴክኒክ ማሠልጠኛ ተቋምን ለማስገንባት የወጣውን ጨረታ እንዲዛባ ማድረጋቸውን ገልጿል፡፡
አቶ ያረጋል የመንግሥትን ግዢ መመርያ መሠረት አድርገው ግልጽ ጨረታ በማውጣት አቅም ያላቸው ተወዳዳሪዎችን በማወዳደር ተቋማቱን በጥራት ማስገንባት ሲገባቸው፣ የክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ከነበሩት አቶ ሀብታሙ ሂካ (በቁጥጥር ሥር ናቸው) ከጥቂት ኮንትራክተሮች ጋር በመመሳጠርና ጨረታው በውስን ጨረታ እንዲፈጸም ትዕዛዝ በመስጠት፣ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ወንጀል ተጠርጥረዋል፡፡
የትምህርት ተቋማቱ መጠናቀቅ የነበረባቸው ውል በተገባበት ከ1998 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በ13 ወራት ውስጥ የነበረ ቢሆንም፣ ከተቋራጮቹ ጋር አስቀድሞ በተፈጠረ ሕገወጥ የጥቅም ግንኙነት ምክንያት፣ ፕሮጀክቶቹ እስካሁን ካለመጠናቀቃቸውም በላይ፣ ለተቋራጮቹ ውል ከፈጸሙበት ክፍያ በላይ ሰባት ሚሊዮን ብር እንዲከፈል ማድረጋቸውን ኮሚሽኑ አረጋግጧል፡፡
አቶ ያረጋል የመንግሥት ተቀጣሪ ሹም እንደመሆናቸው መጠን፣ በሕጋዊ መንገድ ሲያገኙት ከነበረው ገቢ በላይ ያፈሩ ለመሆናቸው አመላካች ማስረጃዎች መገኘታቸውንም ኮሚሽኑ ባደረገው ማጣራት እንደደረሰበት ጠቁሟል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት 7 ቀን 2004 ዓ.ም ባካሄደው በሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ በሁለተኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ፣ የአቶ ያረጋል አይሸሹም ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ የሕግ፣ የፍትሕና የአስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን ጥያቄ በሙሉ ድምፅ በመደገፍ፣ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ መደረጉን በጥቅምት 8 ቀን 2004 ዓ.ም ዕትማችን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/3848-2011-10-22-12-40-07.html