ኢሕአዴግ በሥልጣን ላይ በቆየባቸው ባለፉት 20 ዓመታት ሙስና እየተስፋፋ ነው

(ቢሊሱማ ዜና, ህዳር 7 ቀን 2011) በአገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን የሙስና ወንጀል ለማስቆም መንግሥት ምን እየሠራ ነው? የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ የሚቀርብላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሙስናን መቀነስ የሚቻለው ኅብረተሰቡን በማስተማር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አስራት ግን ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሙስናን በመዋጋት ረገድ ቁርጠኝነት የጐደለው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ኢሕአዴግ በሥልጣን ላይ በቆየባቸው ባለፉት 20 ዓመታት በሙስና ተጠርጥረው የተከሰሱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል የቀድሞ ጠቅላይ ማኒስትር ታምራት ላይኔ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው መታሰራቸው ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ በሙስና ጉዳይ ላይ ቁርጠኛ አቋም እንዳለው የሚያሳይ ነው በማለት አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች በወቅቱ ገልጸው ነበር፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይ መንግሥት ዕርምጃ መውሰዱ በሙስና ወንጀል አንደማይደራደር አመላካች ውሳኔ መሆኑን ያመኑት ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ ይህ የኅብረተሰቡ አመለካከት ግን በሂደት እየተሸረሸረ ሳይመጣ አልቀረም፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት በሙስና ወንጀል የተዘፈቁ አንዳንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ተከታትሎ ለፍርድ የማቅረብ ጉዳይ ትኩረት የተነፈገው ይመስላል፡፡ ባለሥልጣናቱ የፖለቲካ ልዩነት እስካልፈጠሩ ድረስ ያሻቸውን እንዲያደርጉ፣ የፖለቲካ ልዩነት ከፈጠሩ ግን በሙስና ተጠርጥረው የሚታሰሩበት ዕድል ሰፊ መሆኑን የሚናገሩት እነኚሁ ታዛቢዎች፣ ይህንን ሐሳባቸውን ለማጠናከር ከሕወሓት ክፍፍል በኋላ የአቶ ስዬ አብርሃን በሙስና ተጠርጥሮ መታሰር በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡

በአገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን የሙስና ወንጀል ለማስቆም መንግሥት ምን እየሠራ ነው? የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ የሚቀርብላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሙስናን መቀነስ የሚቻለው ኅብረተሰቡን በማስተማር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሰሞኑን ፓርላማ ተገኝተው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራርያ በሰጡበት ወቅትም ይህንኑ ደግመውታል፡፡ መንግሥት የሙስና ወንጀል ስለመፈጸሙ በቂ ማስረጃ ካለው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ወንጀለኞችን ተጠያቂ የማያደርግበት ምክንያት እንደሌለ የገለጹት ጠቅላይ ማኒስትሩ፣ ሙስናን በመቀነስ ረገድ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ከተፈለገ ግን ኅብረተሰቡን ማስተማር ግድ እንደሚል ያስረዳሉ፡፡

የዓረና ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አስራት ግን ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሙስናን በመዋጋት ረገድ ቁርጠኝነት የጐደለው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ሙስና በአገሪቱ ውስጥ ስለመስፋፋቱ ራሱ መንግሥትም የሚያምነው ጉዳይ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ገብሩ፣ መንግሥት ችግር መኖሩን ቢያምንም በተጠርጣሪዎች ላይ ዕርምጃ የመውሰድ አቅምም ሆነ ፍላጐት የሌለው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ የሚታየው ሙስና በከፍተኛ ባለሥልጣናት ጭምር የሚፈጸም ቢሆንም፣ አልፎ አልፎ ‹‹እገሌን አባርሬያለሁ›› የሚል መግለጫ ከመስጠት በስተቀር በግልጽ ሙስና ስለመፈጸማቸው በሚታወቁ ባለሥልጣናት ላይ ዕርምጃ መውሰድ አልቻለም፡፡

‹‹ባለሥልጣናቱ ከመንግሥት ጋር እስከተስማሙ ድረስ ሙስና ቢፈጽሙም ሃይ የሚላቸው ኃይልም ተቋምም የለም፤›› በማለት የፖለቲካ ልዩነት ያላቸው ሰዎች ብቻ ሙስና ፈጽመዋል ተብለው ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ይናገራሉ፡፡

‹‹በሙስና የተዘፈቀ ኃይል ራሱን መልሶ መቅጣት የሚችል አይመስለኝም፤ በሙስና የተዘፈቀውን እዋጋለሁ ቢል የሚጀምረው ከራሱ ነው፤›› በማለት መንግሥት በሙሰኞች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ የተቸገረበትን ምክንያት አቶ ገብሩ ይጠቅሳሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት የመንግሥት ቀኝ እጆችና የሥልጣን መሠረት የሆኑትን እነዚህን ባለሥልጣናት መቅጣት በሥልጣኑ ላይ ስጋት ስለሚፈጥርበት ሊሆን ይችላል መንግሥት ዕርምጃ ከመውሰድ የሚቆጠበው፡፡ ‹‹ነፃነት በሌለበት፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ባልተጠበቁበት፣ የሕግ የበላይነት በሌለበት ሁኔታ ሙስናን መቅረፍ ያስቸግራል፤›› በማለት ሙስና ከፖለቲካ ጋር ተያያዥነት ያለው ጉዳይ መሆኑን አቶ ገብሩ ይገልጻሉ፡፡

አቶ ስየ አብርሃ በሙስና ተጠርጥረው ከታሰሩ በኋላ ሙስና የፖለቲካ ጉዳይ ተደርጐ መወሰዱን የሚናገሩት አቶ ገብሩ፣ በአቶ ስየ ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ‹‹ሙስናን እየፈጸምክ ሥርዓቱን ካልተቀናቀንክ እንደፈለግክ መኖር ትችላለህ፡፡ የእኔን ሥርዓት ከተቃወምክ ግን ሙስና እንኳን ባትፈጽም በሙስና ከስሼ አሳስርሃለሁ፤›› የሚል መልዕክት ያዘለ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

በእርሳቸው እምነት የስየ ‹‹ሕግ›› ተብሎ በአንዳንዶች የሚጠራው ሕግ በችኮላ በፓርላማ ፀድቆ ለፖለቲካ መሣርያነት መዋል ከጀመረ በኋላ፣ ሙስና የመፈክር ጉዳይ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ሙሰኞችም የሚበረታቱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

በአንዳንድ አገሮች ፀረ ሙስና ተቋም የሚቋቋመው ሙስናን ለመዋጋት ቁርጠኝነት አሳይተዋል የሚል እሳቤን ለመፍጠር እንጂ ሙስናን ለመታገል ታስቦ አለመሆኑን የሚናገሩት አቶ ገብሩ፣ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከልቡ ሙስናን ለመዋጋት ከፈለገ ሙስናን ለመታገል የሚያስችሉ መብቶችን ሊያከብር እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡ ከመብትና ከነፃነት ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ያለውን ችግር ሲገልጹም የአንዳንድ አገሮች ሕዝቦች ‹‹ባለሥልጣናቱ የአገሪቱን ሀብት እየመዘበሩ ነው፤›› በማለት፣ ሰላማዊ ሠልፍ ወጥተው ዕርምጃ እንዲወስድባቸው የሚጠይቁ መሆኑን ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ሰላማዊ ሠልፍ መውጣት መንግሥትን ለማፍረስ እንደመሻት ተደርጐ ስለሚታሰብ፣ ይህንን መብት ተጠቅሞ ለውጥ ለማምጣት አለመቻሉን ይገልጻሉ፡፡

ከሕወሓት ክፍፍል በኋላ ሙስናን እንዋጋ የሚለው መፈክር ጐልቶ መውጣቱን የሚያስታውሱት አቶ ገብሩ፣ ሕዝቡ የመንግሥትን ፕሮፓጋንዳ አምኖ ሥር ነቀል ዕርምጃ ይወሰዳል ብሎ የሰነቀው ተስፋ ከተስፋ በላይ አለመዝለሉን፣ እንዲያውም በከፋ መልኩ ሙስና አእየተስፋፋ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡
‹‹አንድ ሙስና የፈጸመ ሰው የመንግሥት ደጋፊ ነኝ እስካለ ድረስ ከአንድ መሥርያ ቤት ወደ ሌላ መሥርያ ቤት እንዲዛወር ይደረጋል፡፡ ወይም ከማዕከላዊ ኮሚቴ ገለል ብሎ ይቆይና ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሌላ ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡ በኢሕአዴግ ጊዜ ሙስኛ ሳይሆን ሙስናን የሚያጋልጠው ነው የሚፈራው፤›› በማለት በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በአዲስ አበባና በሌሎችም ክልሎች በሙስና ተባርረዋል የተባሉ ሰዎች ሹመት አግኝተው ሲንቀሳቀሱ እንደሚታዩ ይናገራሉ፡፡

የአንድነት ለፍትሕና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳም በአቶ ገብሩ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ እርሳቸው ፕሬዚዳንት በነበሩበት በ1989 ዓ.ም. የቀድሞ ድርጅታቸው ኦህዴድ ባደረገው ግምገማ በርካታ የድርጅቱ አባላት፣ ካድሬዎችና የፓርላማ ተመራጮች በሕገወጥ መንገድ ሀብት ማካበታቸው ስለታወቀ ‹‹ከየት አመጣችሁት?›› ተብለው ሲጠየቁ ምንም መልስ መስጠት አለመቻላቸውን የስታወሱት ዶ/ር ነጋሶ፣ ግምገማውን ተከትሎ በሙስና ተዘፍቀው የተገኙ ከአሥር ሺሕ በላይ ካድሬዎች እንዲባረሩና የተወሰኑትም እንዲታሰሩ ቢወሰንም፣ ከአራት ዓመት በኋላ በ1993 ዓ.ም. እነዚያ የተባረሩና የታሰሩ ሰዎች ተፈትተው ወደ ድርጅቱ እንዲመለሱ መደረጉን ይናገራሉ፡፡

ሰኔ 15 ቀን 1993 ዓ.ም. ሥልጣን ከመልቀቃቸው በፊት በነበሩት ቀናት በተካሄዱ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎች ላይ በሙስና በተገኘ ገንዘብ ቪላዎችን እንደሠሩ የሚወራባቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ጉዳይ እንዲታይ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱንም ዶ/ር ነጋሶ ያስታውሳሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ በሙስና ላይ ቁርጠኛ አቋም የሌለው መሆኑንም በግንቦት 1993 የኦህዴድ ስብሰባ ተገንዝበዋል፡፡ በዚሁ የኦህዴድ ስብሰባ ላይ ስብሰባውን ሲመሩት ከነበሩት ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር በሻይ የዕረፍት ሰዓት ላይ በተገናኙበት ወቅት በሙስና የተዘፈቁ ባለሥልጣናት ጉዳይ እንዲታይ ላቀረቡላቸው ጥያቄ፣ ‹‹እያንዳንዱን እየተከታተልን መረጃ የምናገኝበት ሁኔታ አስቸጋሪ ስለሆነ ይህንን [የሙስና] ጉዳይ በሰዎች ላይ ማንሳት ይከብዳል ለውጥ ማምጣት የሚቻለው ኅብረተሰቡን በማስተማር ነው፤›› የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ያስታውሳሉ፡፡ አያይዘውም ‹‹የእኔ አቋም ዕርምጃዎችን ካልወሰድን ሌላውን ኅብረተሰብ የማስተማር ሞራል ሊኖረን አይችልም የሚል ነበር፡፡ ይህ ባለመሆኑም ሙስና ተንሰራፍቷል፤›› በማለት በሙስና ወንጀል የተዘፈቁ ሰዎች ላይ ዕርምጃ አለመወሰዱ ምን ያህል በአገሪቱ ላይ ችግር እንደፈጠረ ዶ/ር ነጋሶ ያስረዳሉ፡፡

የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን የሥነ ምግባር፣ ትምህርትና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አሰፋ በበኩላቸው፣ ሙስና በባህሪው ሚስጥራዊነቱ ተጠብቆ ሥልጣኑና ሀብቱ ባላቸው ታስቦበት የሚፈጸም ድርጊት በመሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት ሙስና ያለበትን ደረጃ በተጨባጭ ለማወቅ እንደሚያስቸግር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ብዙውን ጊዜ በሙስና ላይ ጥናት የሚያደርጉ ድርጅቶች በሰዎች አስተሳሰብ ላይ ተመሥርተው መረጃ እንደሚሰበስቡ የሚናገሩት አቶ ብርሃኑ፣ የሰዎች አስተሳሰብ ቦታ የለውም ባይባልም የእነዚህን ሰዎች አስተሳሰብ ተመርኩዞ በእርግጠኝነት ‹‹ሙስና ጨምሯል ወይም ቀንሷል›› ማለት እንደሚከብድ ያስረዳሉ፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት ፀረ ሙስና ኮሚሸን ከተቋቋመ በኋላ ሙስናን በሚመለከት በአገሪቱ የታየውን ለውጥ በጥናት ማወቅ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ በዓለም ባንክ ድጋፍ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኪሊማንጃሮ ኢንተርናሽናል ከተባለ ድርጅት ጋር በመሆን ጥናት እያካሄደ ነው፡፡ ‹‹[አጥኚዎቹ] የሰበሰቡትን መረጃ የመተንተን ሥራ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ ጥናቱ ሙስና ጨምሯል ወይስ ቀንሷል የሚለውን የኅብረተሰቡ አስተሳሰብ ሊያሳየን ይችላል፤›› ይላሉ፡፡

የአገሪቱ ኢኮኖሚ በሚንቀሳቀስበትና ብዙ ገንዘብ ወጥቶ በርካታ የልማት ሥራዎች በሚከናወኑበት ጊዜ የሙስና አጋጣሚዎች እየሰፉ ሊሄዱ እንደሚችሉ የሚጠበቅ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ብርሃኑ፣ ችግሩን ለመቅረፍ ጥናቱን አይቶ መወሰን እንደሚጠይቅ ይናገራሉ፡፡

አቶ ብርሃኑ እንደሚሉት ኮሚሽኑ በተቋቋመ በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ ሙስናን በመከላከልና ሕግ በማስከበር ረገድ መልካም ውጤቶችን ያስመዘገበ ቢሆንም፣ ኅብረተሰቡ በሚጠብቀውና ኮሚሽኑ በሚያስመዘግበው ውጤት መካከል ክፍተት ስላለ ጠንክሮ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽን በሙስና ወንጀል የተዘፈቁ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ከሶ ወደ ፍርድ የማቅረብ አቅም የለውም ተብሎ በአንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች የሚሰነዘሩት ትችቶችም መሠረተ ቢስ ውንጀላ መሆናቸውን አቶ ብርሃኑ ይገልጻሉ፡፡

‹‹አንድ ሰው ባለሥልጣን ስለሆነ የግድ መክሰስ ያለብን አይመስለኝም፡፡ ጉዳዩ የሚያስጠይቀው ከሆነ ማንም ሰው ይጠየቃል፡፡ ከዚህ ቀደምም ሆነ በቅርቡ የጠየቅናቸው ባለሥልጣናት አሉ፡፡ ባለሥልጣን ለመክሰስ ብቻ ብለን ግን የምንሠራው ሥራ የለም፤›› በማለት ኮሚሽኑ ሰዎችን የሚከሰው በሙስና ወንጀል ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ ሲያስብና መረጃ ሲኖረው ብቻ መሆኑን ያብራራሉ፡፡

By bilisummaa