(ቢሊሱማ, ህዳር 14 ቀን 2011) በዘረኛውና ፋሽስቱ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀውን ግንቦት 7ን በመምራት፣ የዘረኛውና ፋሽስቱ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትና መንግሥት ለማፈራረስና የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል በሚል ክስ ተመሥርቶባቸው በሞት እንዲቀጡ ውሳኔ የተላለፈባቸው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ፣ 24 ተጠርጣሪዎች በሽብር ወንጀል ጥቅምት 30 ቀን 2004 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ክስ የተመሠረተባቸው ኢትዮጵያን ለማተራመስ አቅዶ ከሚንቀሳቀሰው የኤርትራ መንግሥት፣ የሎጀስቲክስ፣ የወታደራዊና የፋይናንስ ድጋፍ በሚደረግለትና ከኦብነግና ከኦነግ ጋር ጥምረት በመፍጠር፣ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ጦርነትን በአማራጭ ካስቀመጠው የግንቦት 7 አሸባሪ ድርጅት ውስጥ አመራርና አባል በመሆን እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የክስ ቻርጁ ያብራራል፡፡
ተከሳሾቹ አባል በሆኑበት ግንቦት 7 ድርጅት ውስጥ ሆነው የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትን በኃይል በማናጋትና በማፈራረስ፣ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለማድረስ በማሰብ በጋራ የወንጀል አድማ ስምምነት ማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡
ክሱ ከተመሠረተባቸው 24 ግለሰቦች መካከል አንዱዓለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ ዮሐንስ ተፈራ፣ የሽዋስ ይሁን ዓለም፣ ክንፈ ሚካኤል አበበ፣ ምትኩ ዳምጤ፣ እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አያሌው በእሥር ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ውቤ ሮቤ፣ ኤፍሬም ማዴቦ፣ መስፍን አማን፣ ዘለሌ ጸጋ ዘአብ፣ ፋሲል የኔዓለም፣ አበበ በለው፣ አበበ ገላው፣ ነአምን ዘለቀ፣ ኤልያስ ሞላ፣ ደሳለኝ አራጌ፣ ኮሎኔል አለበል አማረ፣ ኦባንግ ሜቶ፣ መስፍን ነጋሽና አብይ ተክለ ማርያም በሌሉበት የተከሰሱ ናቸው፡፡
ሁሉም ተከሳሾች የወንጀል ድርጊቱን ዓላማ፣ ግብና ውጤቱን ሙሉ በሙሉ በመቀበል፣ በአመራር፣ በሽብር ፈጻሚነትና አስፈጻሚነት፣ የሽብር ተልዕኮ በመስጠትና በመቀበል፣ የሽብር ድርጊቶችን በመፈጸም፣ በማሴር፣ በማቀድ፣ በማነሳሳትና የውጭና የአገር ውስጥ የሽብር መረብ በመዘርጋት፣ አባላትን በመመልመልና በህቡዕ በማደራጀት የሽብር አፈጻጸም፣ የግንኙነትና አደረጃጀት መመርያዎችን በማጽደቅ፣ በመምራት፣ አባሎቻቸውን ወደ ኤርትራ በመላክ፣ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ከወሰዱ በኋላ ወደ አገር ውስጥ ተመልሰው ሰርገው እንዲገቡ ማድረጋቸውን የክሱ ዝርዝር ያስረዳል፡፡
ተከሳሾቹ ህቡዕ ግንኙነት በመፍጠርና በመቀናጀት ለሽብር ሴራቸው ሕገ መንግሥታዊ የመደራጀትና ሐሳብን በነፃ የመግለጽ መብትን ሽፋን በማድረግ፣ የሽብር ጥሪዎችን በኤርትራ ሚዲያዎችና በውጭ አገር ለሽብር ተግባር ባቋቋሟቸው ኢሳት ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ ኢንተርኔትና የተለያዩ የመረጃ አውታሮችንና በፓልቶክ የሚደረግ የሽብር ቅስቀሳ ሥራ ለመሥራት መስማማታቸውንም ክሱ ይጠቅሳል፡፡
የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍተሕ ፓርቲ (አንድነት) ምክትል ሊቀመንበርና ቃል አቀባይ አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ የፓርቲው አባል አቶ ናትናኤል መኮንን፣ የመደራጀት መብትን እንደ ሽፋን በመጠቀም፣ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ የግንቦት 7 የአገር ውስጥ የሽብር ቡድን የወጣቶች አደረጃጀት ኃላፊና ወኪል በመሆን በኤርትራና በውጭ አገር ካሉ የድርጅቱ አመራሮች ጋር በህቡዕ በመገናኘት የሽብር ተልዕኮ በመቀበልና በማስተላለፍ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደነበሩ ክሱ ያብራራል፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሐሳብን በነፃ የመግለጽ መብትን እንደሽፋን በመጠቀም ጊዜው ተለይቶና በውል ባልታወቀ ሁኔታ፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በተደራጀ የሽብር ድርጊት ለማፈራረስ፣ ከግንቦት 7 አመራሮች ጋር በህቡዕ ግንኙነት በማድረግና የአገር ውስጥ ወኪል በመሆን የሽብር ተልዕኮ በመቀበል በአገር ውስጥ ከተደራጀው የሽብር ቡድን አባላት ጋር በመተባበርና የሽብር ዕቅድ በመንደፍና የሽብር ዓላማ ያላቸውን ስብሰባዎች በመምራትና ውሳኔዎችን ያስተላለፈ መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡
በሌሉበት ከተከሰሱት ውስጥ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ የግንቦት 7 ድርጅት ዋና ጸሐፊና ሊቀመንበር መሆናቸውን፣ አመራርና የሽብር አቅጣጫ በመስጠትና የተለያዩ የሁከት ጥሪዎችንና ንግግሮችን በማድረግ ወንጀል ሲከሰሱ፣ ሌሎቹ የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚና አመራር በመሆን በውጭና በአገር ውስጥ አባላትን በመመልመልና በተለያዩ ተሳትፎዎች መከሰሳቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡
የቀድሞው የአዲስ ዜና ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም፣ የኢሳት ዋና አዘጋጅና የግንቦት 7 ድርጅት አመራር በመሆን፣ አባላትን በመመልመል፣ በቴሌቪዥን መመርያ በመስጠትና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ፣ ተወዛዋዥና ድምፃዊ አበበ በለው ደግሞ የኢሳት ቴሌቪዥን የቦርድ አመራርና ቃል አቀባይ በመሆን የሽብር ድርጊቱን እንዲፈጸም ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን የክስ ቻርጁ ያብራራል፡፡
በሽብር ወንጀል ሊከሰሱ መሆኑ መረጃ እንደደረሳቸው በመግለጽ ከአገር ከተሰደዱት የአዲስ ነገር ጋዜጠኞች መካከል፣ የጋዜጣው ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽና በእንግሊዝ አገር ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ትምህርቱን በመከታተል ላይ የሚገኘው የጋዜጣው ማኔጂንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ አብይ ተክለ ማርያም በሽብር ወንጀል ክሱ ውስጥ ተካተዋል፡፡
ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽና አብይ ተክለ ማርያም የተከሰሱት፣ የኢዲስ ነገር ድረ ገጽ በሆነው አዲስ ነገር ኦንላይን ዶት ኮም ላይ በአሸባሪነት የተሰየሙትን የግንቦት 7 ድርጅት፣ ኦነግ፣ ኦብነግን እንዲሁም በሕጋዊ መንገድ የመደራጀትና የነፃ ፕሬስን ሽፋን በማድረግ በሽብር ድርጊት ተሳትፈው የተገኙትን ግለሰቦች፣ የጥፋትና የአመፅ ዓላማቸውንና ተግባራቸውን ዕውቅና በመስጠት የልምድ ድጋፍ በማድረጋቸው መሆኑን ክሱ ያብራራል፡፡
የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክሱን ለፍርድ ቤቱ ሲያቀርብ፣ የአንድነት አባል አቶ ናትናኤል መኮንን የሚያመለክተው እንዳለው ለፍርድ ቤቱ ገልጾ ሲፈቀድለት፣ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕላዊ) ከፍተኛ የሆነ የሞራልና የአካል ጉዳት እንደደረሰበት ተናግሯል፡፡ ግለሰቡ ልብሱን እንዲያወልቅ ተደርጎ ውኃ እየተደፋበት መገረፉን፣ ለሰባት ቀናት ያለ ምግብ መቆየቱን፣ ለ23 ቀናት እጁ ወደኋላ ታስሮ መቆየቱንና ከቤተሰቦቹ ጋር አለመገናኘቱን፣ መርማሪዎች ያሉትን ካልፈጸመ እንዳይተኛ መደረጉን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በማዕከላዊ እሥር ቤት ተገኝቶ እሥረኞችን መጎብኘቱንና በእሥረኞቹ ላይ ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጠው መግለጫ ከእውነት የራቀና እሱን (ናትናኤልን) የማይወክል መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ገና ክሱን መቀበሉ መሆኑን አስታውቆ፣ ማንኛውንም ቅሬታ ማቅረብ የሚቻለው ክሱ ከተነበበና ክርክር በሚጀመርበት ወቅት መሆኑን በመግለጽ፣ አቶ ናትናኤልም በዚያን ወቅት ያለውን ቅሬታ ማቅረብ የሚችል መሆኑን አስታውቋል፡፡
ሁሉም የተከሰሱበት ወንጀል ከወንጀል ሕግና ከሽብርተኝነት አዋጅ አንፃር፣ የዋስ መብት የሚከለክል መሆኑን በመግለጽ፣ ጠበቃ ማቆም የማይችሉ ሦስት ተከሳሾች፣ ሀብት ንብረት እንደሌላቸውና ጠበቃ ማቆም እንደማይችሉ መሐላ እንዲፈጽሙ በማድረግ፣ ክሱን ለመስማት ለኅዳር 5 ቀን 2004 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ አብቅቷል፡፡