(ቢሊሱማ፣ 29 ሚያዝያ 2012) የዘረኛው መለስ ዜናዊ አገዛዝ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ያቀረበውን የመብት ጥያቄ በሃይል ለመጨፍለቅ በአዲስ አበባ የሚገኙትን የምዕራብ ዲፕሎማቶች አንድ በአንድ እየተገናኘ አገሪቱንና የቀጠናውን ሰላምና መረጋጋት ሊያደፈርስ የሚችል የእስልምና አክራሪነት መረብ በአገሪቱ መዘርጋቱን እየሰበከ እንደሚገኝ ታውቆአል።
እንደ ታማኝ ምንጮቻችን መረጃ ከወያኔ ቱባ ባለሥልጣናት አንዱ የሆነው ስዩም መስፍን ለሃያ አመታት የመራውን የውጪ ጉዳይ ሚንስትርነት ሥልጣኑን ለቆ የወያኔ ባለሥልጣናትና የንግድ ድርጅቶቻቸው የአገሪቱን ገንዘብ ወደሚያሸሹበት አዲስቷ ሸሪክ አገር ቻይና ሲመደብ ለይስሙላ ለተተካው ሃይለማሪያም ደሳለኝ በታኮነት የተቀመጠው ብርሃኔ ገብረኪርስቶስ ፤ በአዲስ አበባ የሚገኙትን የምዕራብ ዲፕሎማቶች አንድ በአንድ እየተገናኘ አገሪቱንና የቀጠናውን ሰላምና መረጋጋት ሊያደፈርስ የሚችል የእስልምና አክራሪነት መረብ በአገሪቱ መዘርጋቱን እየሰበከ እንደሚገኝ ታውቆአል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰፈነው የፖለቲካ አፈና በተጨማሪ የኑሮ ውድነቱ እያስከተለ ባለው ማህበራዊ ቀውስ አንድ ቀን ሊፈነዳ የሚችል ህዝባዊ አመጽ እንደሚኖር በመገመት ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተሉ ያሉ ምዕራባዊያን ዲፕሎማቶች በመለስ ዜናዊ አገዛዝ ላይ የነበራቸውን እምነት እንደሸረሸረው በዚህም የተነሳ የብርሃኔ ገብረ ክርስቶስን ውትወታ ምንም ቦታ እንዳልሰጡት ገልጸዋል።
መለስ ዜናዊ ባለፈው ሳምንት ለፓርላማ ተብዬው ስብስብ በሰጠው መግለጫ የሙስሊሙን የመብት ጥያቄ የጥቂት አክራሪዎች ጥያቄ ነው ከማለት አልፎ “የአልቃይዳ ህዋስ በአገሪቱ ውስጥ መኖሩ ተደርሶበታል” ማለቱ ብዙዎችን እንዳስቆጣና ባለፈው አርብ ቁጥሩ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በተቃውሞ በነቂስ እንዲወጣ እንዳደረገው ታውቆአል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የተባለው በህዝበ ሙስሊም ተቃውሞ የገጠመው ተቋም እንደርሱ በተለያዩ ክልል ከህዝብ የተነጠሉ ኡላማዎችን ሰብስቦ፣ ከዞን እና ከወረዳ ምክር ቤት ሀላፊዎች ጋር በጋራ ተመካክሮ ባሳለፈው አቋም፣ የአክራሪነት መንፈስ የተጠናወታቸው አካላት ህዝበ ሙስሊሙ ሀይማኖቱን ተረጋግቶ እንዳያካሂድ እያደረጉት በመሆኑ፣ ህብረተሰቡና የጸጥታ አስከባሪዎች ግለሰቦቹን እየያዙ ለህግ ማቅረብ እንዳለባቸው ሰሞኑን ውሳኔ ማስተላለፉ መለስ ዜናዊ ሊወስደው ላሰበው የሃይል እርምጃ መሰናዶ እንደሆነ ይነገራል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው የወያኔን ጣልቃገብነት በሃይማኖቱ ውስጥ እያስተናገዱ ያሉት ሼህ አህመዲን ሼህ አብዱላሂ ባለድርሻዎች አክራሪዎችን እየመረጡ ወደ ህግ እንዲያቀርቡዋቸው መጠየቃቸው በርካታ የሙስሊም እምነት ተከታዮችን እያስቆጣ ነው።
በመላው አገሪቱ የሚገኙ የሙስሊም እምነት ተከታዪች በአወሊያ የተነሳውን ህዝባዊ ጥያቄ በመደገፍ ድጋፋቸውን እየገለጹ እንደሆነ የገለጸው ዘጋቢያችን ባለፈው አርብ አርሲ አሳሳ፤ በደሴ፤ በጂማና በሃረር በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወጥተው ድጋፋቸውን መግለጻቸውን አስታውሶአል።
በአርሲ አሳሳ የመንግስት ታጣቅዎች በወሰዱት እርምጃ ሶስት ሰዎች መገደላቸዉምተዘግቦአል::